@mamamesayi
iAccount based inUnited States
About this account
- Account based in
- United States
- Connected via
- United States App Store
Account-level information from X, not a live location or the device used for a specific post.
News anchor
Alexandria, VA
Joined August 2011
- Tweets1.2K
- Following326
- Followers249K
- Likes20
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ኦላ ያወጣው መግለጫ ሁለት መልኮች ያሉት ነው። በትብብር ሃይሎች ውስጥ አብሮ እየሰራ እንደሚገኝ በይፋ መግለጹ የብዙዎችን ጥርጣሬ የገፈፈና በተለይ በእነጃዋር ሰፈር ያልተጠበቀ ዱብ እዳ የሆነ አቋም ነው። ጃዋር የኦላን አቋም ሊያንቆለጳጵሰው የሄደበት መንገድ ፖለቲካዊ ድምጸቱ እየደከመ መምጣቱን የሚያሳይ ነው። እንዳልተከፋ ለመምሰል የወለጋዋን ጉዳይ በማጦዝ የኦላን መግለጫ አውዱን ለመቀየር ሲጋጋጥ ሳየው ገርሞኛል። በኦላ መግለጫ ሌላው መልክ ሆኖ የተከሰተው ለፋኖ ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ ነው። ብስልን ከጥሬ የደበላለቀ አቋም የሆነብኝም ለዚሁ ነው። ትብብር ውስጥ የገባው እኮ እንዲህ ዓይነቱን ልዩነት በንግግር ለመፍታት ነው። ነገ ወንበር ስበው ተቀምጠው የሚፈቷቸው ሺህ ጉዳዮች እኮ አሉ?!
ፋኖም ከኦላ ጋር ለመሰራት ሲወስን ኦላ ቅዱስ ስለሆነ አይደለም። ሚሊየን የሚያሳስቡ ጉዳዮችን ይዞ ነው ወደ ትብብሩ የገባው። ኦላ ወደ ትብብር መምጣቱ መልካም ጅምር ሆኖ ያቀረበው ቅድመ ሁኔታ የቡድኑን አለመረጋጋት የሚያሳይ ነው። ሁሉም የትብብር ሃይሎች የየራሳቸው ጥያቄዎች አሏቸው። እነዚህ ጥያቄዎች የሚፈቱበት ማዕቀፍ አዘጋጅተው በቅድሚያ መከናወን ያለበት ላይ ትኩረት ማድረግ የትብብር ሀሁ እንደሆነ ለኦላ ተሰውሮበት ወይስ የእነጃዋር ጩኸት አስደንግጦት? ደግሞም በትብብር ውስጥ ውይይት እያደረጉ እዚያው መነጋገር ሲቻል የሆኑ ወገኖችን ለማስደሰት በሚል በትብብሩ ሂደት ላይ ጥርጣሬን መፍጠር ትልቅ ፋወል ነው። ከማንም በላይ ኦላን ይጎዳል። ለሁሉም ጊዜ አለው እንደሚባለው ኦላ ያለጊዜው የሳበውን አጀንዳ ለሚቀጥለው የትብብሩ ምዕራፍ ቢያቆየው ይበጃል። እነጃዋር በአርቴፊሻል ደስታ የሚፈነድቁት እውነተኛውን ደስታ መቼም ስለማያገኙት ነው።
በጉራጌ አበሸጌ ወረዳ የሚፈጸመውን የንጹሃን ግድያ በተመለከተ የእነጃዋር ጎራ ጩኸት ቀምቷል። አማራ አማራውን እየገደለ ነው የሚል የሞኝ ተረክ ይዘው ተሽቀዳድመው መድረኩ ላይ እሪታውን አቅልጠውታል። የአዞ እምባ። እንደጅራፍ ራስ ገርፎ ራስ መጮህ። እንግዲህ የሚገደሉት በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች ናቸው። ታፍነው የተወሰዱትም የአማራ ተወላጆች ናቸው። ቤት ንብረታቸው እየተቃጠለ የሚገኘው የአማራ ተወላጆች እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ ነው። የሚገርመው ይህን የሚያደርጉትም በእነ ጃዋር ስሌት የአማራ ተወላጆች ናቸው። ይህን ለመናገር ይሉኝታ የሚባል እንኳን የሚከለክላቸው አይደለም።
የፋኖ ታጣቂዎች፥ አዲስ አበባን ተሻግረው ነው አበሸጌ ላይ የገዛ ወገናቸውን የሚጨፈጭፉት? ወይስ በፓራሹት ከሰማይ ወርደው ነው ጥቃቱን የፈጸሙት? በቅርቡ የአከባቢው ባለስልጣናት የአበሸጌውን ጥቃት የሚፈጽሙት መነሻቸው ከኦሮሚያ ክልል የሆኑ ኦሮምኛ ተናጋሪ ታጣቂዎች ናቸው ብለው መግለጫ ሰጥተዋል። እነዚህ ባለስልጣናት ብልጽግንናዎች ናቸው። የሽመልስ አብዲሳ ታጣቂዎች እንደሆኑ በተደጋጋሚ በማስረጃ ተደግፎ የቀረበ ጉዳይ ነው። በሲዳማ አጎራባች ወረዳዎችም ተመሳሳይ ጥቃት የሚፈጽሙት እነዚሁ ናቸው። ሀቁ ይሄው ነው። እውነቱን እንደካልሲ ገልብጠው ሊነግሩን መፈለጋቸው የሚደንቅ ነው። እንደው ምን ያህል ቢንቁን ነው ፋኖ አበሸጌ ላይ የአማራ ተወላጆችን ገደለ ብለው ለመናገር የደፈሩት? ቀድሞ በመጮህ የሚቀየር እውነት ግን የለም። ይኸው ነው።
አንዳንድ ነገሮች
አብይ አህመድ ከአፈርኩ አይመልሰኝ ዓይነት ብሽሽቅ ውስጥ ገብቷል። ህንድ በብሪክስ ስብሰባ አጋጣሚ የተናገራት እንግሊዘኛ የማህበራዊ መድረኩ ማድመቂያ መሆኗ ሳይበርድ እልህ ውስጥ እንዳለ በሚያሳብቅ መልኩ ራሱኑ ደግሞታል። 7ዓመት የእድሜ ቅናሽ ከፈለጋችሁ ኢትዮጵያ ኑ - ሲል ጥሪ አድርጓል። ስለዲስካውንት አጠገቡ ያሉ የኢኮኖሚክስ አማካሪዎች ትንሽ ገለጣ ቢጤ ቢያደርጉለትና ይህቺን ቃል በሌላ እንዲተካ ደግሞ እንግሊዘኛው ላይ የሚራቀቁት እነቢልነኔ ስዩም የሆነ ኮርስ ቢሰጡት ጥሩ ነበር። ቋንቋ አለመቻል ትልቅ ነገር ሆኖ አይደለም። እሱ ግን ትልቅ አድርጎት ተመላልሶ በስህተት ላይ ስህተት እየደራረበ ነው። እልኸኛና ከህዝብ ጋር ብሽሽቅ ውስጥ መግባት ስለሚወድ እንጂ በድጋሚ በተመሳሳይ ስህተት መከሰት አልነበረበትም። ሞኝ ባያፍር የሞኝ ዘመድ ያፍር እንዲሉ ዘመዱ ካላችሁ ሀፍረታችሁን ግለጹለትና ወደሌላ አጀንዳ አስገቡት። ወርዶ አስወረደን እኮ ሰውዬው።
ትምህርት ሚኒስቴር በትግራይ ተማሪዎች እንደማይመደቡና በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ጊዜያዊ ምደባ እንደሚሰጣቸው አስታውቋል። በአንጻሩ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ''ምንም ችግር የለም፥ ተማሪዎቼን ልቀበል ተዘጋጅቼአለሁ'' ሲል መግለጫ አውጥቷል። የአብይ አህመድ ዘመን የቀውስና የአለመረጋጋት ዘመን ለመሆኑ አመላካች ከሆኑ አያሌ ክስተቶች እንደአንዱ አድርጎ ማየት ይቻላል። የፕ/ር ብርሃኑ ውሳኔ ብልጽግና ለጦርነት ዝግጅቱን አጠናቆ ከድሮን ጥቃቱ ባሻገር ይፋዊ ጦርነት ውስጥ ሊገባ እንደሆነ ጠቋሚ ነው። በእርግጥ ከፊታችን ጦርነት ስለመኖሩ ብዙ ምልክቶች ከወዲሁ እየታዩ ነው። ይህ የሚመጣው ጦርነት ግን እንደከዚህ ቀደሞቹ ህዝብ በልቶ፥ የሀገር አንጡራ ሀብት አውድሞ ብቻ የሚጠናቀቅ አይደለም። ኢትዮጵያ ላይ የስርዓት ለውጥ ሊያመጣ የሚችል እንደሆነ መተንበይ ከባድ አይደለም። የሆነ ደፍርሶ የሚጠራ ነገር ይኖራል። ጦርነቱን የሚጀምሩ መሪዎች ቢኖሩም መጨረሻው ግን እነሱንም ታሪክ አድርጓቸው የሚጠናቀቅ እንደሚሆን ለመግለጽ ጠንቋይ ወይም መጽሀፍ ገላጭ መሆን አይጠበቅብንም። ለማንኛውም ኢትዮጵያችንን ከክፉ ሁሉ እንዲጠብቃት እንጸልያለን።
የጃዋር መሀመድ ነገር እርግጡ ታውቋል። በስሱ ያጠለቃት ማስክ ወልቃለች። ክንብንቡን ገልጦ በበፊት ማንነቱ ተከስቷል። አዲስ ነገር አይደለም። ይህ ሊመጣ እንደሚችል የገመቱ ጥቂቶች አይደሉም። ቄሮ እንደበፊቱ በምድር መንገድ አይዘጋም፥ ወደ ሰማይ ወጥቶ በድሮን አፈር ከድሜ እያስጋጠ መሆኑን በነገረን በሰሞኑ የቲክታክ መድረኩ ማን ቀድሞ ከመኮንኖች ክበብ ቢራ እየተጎነጨ ጎልፍ እንደሚጫወት ፍንጩን አሳይቶናል። ጃዋር ወደእናት ቤቱ ነው የተመለሰው። ከዚያ ተለቅና ገዘፍ ባለ የፖለቲካ ስብዕና ለጠበቅነው በእርግጥ ፍሬቻ ሳያበራ መታጠፉ በትንሹ ሊያስገርመን ይችላል። የፖለቲካ አክሮባት ነፍሱን እንደምታስደስታት ጠፍቶን አይደለም ያን እምነት የሰጠነው። ሰው ነውና ከጥፋቱ ተምሮ እውቀቱን ለመልካም ነገር ያውላል በሚል ሚጢጢዬ ተስፋ እንጂ የጃዋር ልብ ወዴት እንደሚመታት አጥተነው አልነበረም። ለማንኛውም ጃዋር ተሰብስቧል። ወደ ምሽጉ ገብቷል። የኦህዴድ መንገድ የብርሃን መንገድ ነው ብሎ እየሰበከ ነው። መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት።
ለማንኛውም እንኳን ለአዲሱ ዓመት አደረሳችሁ። የቁጥር ለውጥ ብቻ እንደሆነ ቢገባኝም ወግ ነውና እንኳን አደረሳችሁ ማለቱ አይከፋም። 2018 ለኢትዮጵያውያን የመከራ ዘመን ሆኖ አልፏል። ወገብ ከሚያጎብጠው፥ ትከሻ ከሚያዝለው፥ እንደግዙፍ ቋጥኝ ከከበደው የኑሮ ውድነት በተጨማሪ በሰላም እጦት ስቃዩን ሲያይ፥ ፍዳውን ሲበላ ነው 2018ትን ያሳለፈው። ላዩ ላይ የተጫነበት፥ እንደአልቅት ተጣብቆ ደሙን እየመጠጠ ባለው የአብይ አህመድ አገዛዝ የኢትዮጵያ ህዝብ የሰማዩን ሲዖል እዚሁ ምድር ላይ እየኖራት ነው።
ትግራይ፥ አማራ፥ ከፊል ኦሮሚያ፥ ጋምቤላ፥ ቤንሻንጉል፥ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በረሃብና ሰላም እጦት ለአንድም ቀን ፋታ ሳያገኙ የከረሙበት አመት ሆኖ ነው 2018 ያለፈው። አሁንም መከራው አለ። የዘመን ቁጥር ተቀይሮም ስቃዩ አልቆመም። አዲስ አመት እንጂ አዲስ ነገር የለም። አሁንም ሰውዬው አለ። ዘንድሮም ፈርኦን ከዙፋኑ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ሊመልስ የሚገባው ጥያቄ 2020 ዓመተ ምህረትን የሚቀበለው በዚሁ ሁኔታ ነው? ወይስ በጥርሳችንም፥ በጥፍራችንም ቢሆን ታግለን ይህን የዘመን እርግማን የሆነን ስርዓት ከላያችን ላይ አሽቀንጥረን በመጣል በነጻነትና በአዲስ መንፈስ እንሻገረዋለን?
ዘመኑን የትግል ያድርግልን! 2020 ላይ በደማቅ ሁኔታ፡ ነጻነት አግኝተን፥ እኩልነት ሰፍኖ፥ ሰላም ምድሪቱን ወርሶ፥ ለማክበር ያብቃን!
በሪዮት ሚዲያ ጃዋር መሀመድ ያደረገውን ቆይታ አዳመጥኩት። ቃለመጠይቁን ቴዲ ጸጋዬ በተሻለ ሁኔታ አቅርቦታል። እንደባለፈው ሜዳውንም ፈረሱንም ለጃዋር አለቀቀለትም። የትላንቱ የጃዋር ቆይታ 50 በመቶ ማስመሰል፥ 30 በመቶ መመጻደቅ፥ 20 በመቶ ደግሞ ማደናገር ሆኖ የተጠናቀቀ ነው። ጃዋር በትብብሩ ዙሪያ ያሳየው አቋም በተለይም በመርህ ደረጃ ትብብር ያስፈልጋል እያለ የሚተነትነው አንድም እውነት አይደለም ወይም ልቡ ውስጥ የሌለን ነገር ነው የሚነግረን። ጃዋር ከአብይ ባልተናነሰ የትብብሩን ውድቀት የሚመኝ፥ ውስጥ ለውስጥም አድምቶ የሚሰራ ስለመሆኑ ከጥርጣሬም በላይ መግለጽ ይቻላል። ትብብሩ ኦህዴድ/ብልጽግናን ያፈርሰዋል። ያን ደግሞ ጃዋር ፈጽሞ አይፈልግም። በሪዮት ሚዲያ ላይ ትብብሩ የተጋለጠ ነው፥ ፍኖተ ካርታ የለውም ምናምን በሚሉ ሰበብ ምክንያቶች መደበቅ መፈለጉን በግልጽ አይቼአለሁ። ስለትብብሩም ሆነ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ያነሳቸው ሀሳቦች ቅብ ናቸው። ማስመሰል እንጂ ሀቀኝነት የሚታይባቸው አይደሉም።
ሌላው 30 በመቶ የቃለመጠይቁ ክፍል መመጻደቅ የሚታይበት ነው። ጃዋር ኢጎው ሰማይ ጥግ የደረሰ መሆኑን በግልጽ አይቼበታለሁ። በመመጻደቅ ነው ብዙዎቹን ጥያቄዎች ሲመልሳቸው የነበረው። ለአብነት ከልደቱ ለቀረበለት የእንከራከር ጥያቄ ምላሹን እንዲያቀርብ በቴዲ ሲጠየቅ የመለሰበት መንገድና የአንገጋር ቅላጼው በጉራ የተጀቦነ፥ እልም ያለ ተመጻዳቂነት የሚታይበት ነበር። በሌሎች ጉዳዮች ላይም ይኸው ባህሪው ሲንጸባረቅበት ነበር። ያኔ ታማኝ በየነ የአብረን እንስራ ጥሪ ሲያደርግለት ''ምግቡን ብሉ ሂሳቡን እኛ እንከፍላለን'' በሚል የሰጠውን ምላሽ አስታወሰኝ። ትንሽ ጭብጨባ ሲሰማ የሚቆለለው ነገር ሁሌም ይገርመኛል። በመንጋ ሙቀት ውስጥ ሲቆይ ስሜቱን መቆጣጠር እንደማይችል ቢታወቅም እድሜና የገዛ ስህተቱ ያስተምረዋል የሚል ተስፋ ነበረኝ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው ባህሪው ግን እድሜ ቁጥር እንጂ ብስለትን እንደማያመጣ የሚያሳይ ነው እንዴ የሚል ጥያቄ እንዳነሳ የሚያደርገኝ ሆኗል።
የቀረው 20 በመቶ ደግሞ የተለመደው አደናጋሪና ሀሰተኛ መረጃዎችን ማሰራጨት ነው። ስለፋኖ እኝኝኝኝ ሲልበት የከረመውን ልብወለዱን በእጥፍ ጨምሮ መጥቷል። ቢቢሲን ሀሰተኛ፥ እሱን ደግሞ እውነተኛ አድርጎ ያቀረበበት ሁኔታም የጃዋርን የማደናገር አካሄድ እርቃኑን ያሳየ ነበር ማለት ይቻላል። በወለጋው ዕልቂት ዙሪያ መሬት ላይ ባሉ እማኞችና በተለያዩ የመረጃ ማሰባሰቢያ መንገዶች ቢቢሲ ሰሞኑን የሰራውን ዘገባ ጃዋር ''ቢቢሲ ተሳስቷል። ትክክለኛው መረጃ የእኔ ነው'' ሲል አይኑ እንኳን አይርገበገብም። እሱ ከሚነግረን ውጪ ያሉ መረጃዎችን ሀሰተኛ እንደሆኑ ለመናገር ቅንጣት ማመንታት አይታይበትም። መረጃዎችን ሲበርዝ፥ ሲያፋልስና ከአውዱ ውጪ ሲያቀርባቸው በእርግጥ ቴዲ ጸጋዬም እየተከተለ ሲሞግተው ነበር። ለማንኛውም ጃዋር በጽኑ ሰግቷል። እየቀረበ የመጣው የትብብር ድምጽ ረብሾታል። በጥርሱም ዘንጥሎ፥ በጥፍሩም ቧጭሮም ቢሆን ትብብሩን ማኮላሸት ቢችል ምንኛ ደስ ባለው?!
ጃዋር አሁንም ካልኩሌተሯን ከእጁ እንደያዘ ነው። ያቺን ላፕቶፑን ለአቶ ለማ መገርሳ የሰጠ ጊዜ ካልኩሌተሯንም አሽቀንጥሮ የወረወራት መስሎን ነበር። ለካንስ ለክፉ ጊዜ ''መዥረጥ'' የምትደረግ መሆኗን አላወቅንም ነበር። ያኔ የኢህአዴግ ስልጣን ሲንገዳገድና ወደ ገደል አፋፍ ሲቃረብ ጃዋር የስርዓቱ መውደቅ ሀገረ መንግስቱን ያፈርሰዋል የሚል አቋም ያዘና ኦህዴድን ወደፊት በማምጣት ኢህአዴግ ቁጥር 2 ስልጣኑን እንዲይዝ ካልኩሌት አደረገ። ውስጥ ካለው የኦህዴድ መዋቅር ጋር በመስራት፥ በብአዴን ትከሻ ላይ የኦህዴድ/ብልጽግና መንግስት እንዲመሰረት ሚናውን ተጫወተ።
በወቅቱ የእሱ ምርጫ አብይ አህመድ ባይሆንም በሂደት እንፈነግለዋለን በሚል ተስፋ አድርጎ ስርዓተ መንግስቱን በማጽናት ላይ ሰፊ ዘመቻ ከፍቶ ነበር። ኋላ ላይ አብይ አህመድ በካልቾ ብሎ ወደ ወህኒ ወረወረው እንጂ። አንድ ወቅት ላይ ከእስር ከወጣ በኋላ በአብይ አህመድ ላይ አኩርፎ እያለ ስለአብይ የተናገረውን ምን ጊዜም አስታውሰዋለሁ። ስልጣኑ ከኦሮሞ እጅ ወጥቶ ሌላ ከሚወስደው አብይ እንደያዘው እንዲቆይ ማድረግ አለብን - ማለቱን አንዘነጋውም። ያን ጊዜ ስርዓተ መንግስቱን ከስሩ መንግለን ብናስወግደው ኖሮ ዛሬ የኢትዮጵያ ታሪክ በተቀየረ ነበር።
አሁንም ጃዋር ሀገረ መንግስቱ እንዳይፈርስ ስርዓተ መንግስቱን እንጠብቀው ዓይነት አቋም ይዞ ዳግም ወደ መድረኩ መጥቷል። ችግሩ የአንድ ግለሰብ ነው እያለን ነው። አሁንም ጥገናዊ ለውጥ እንጂ ስርነቀል ለውጥ ሀገር ያፈርሳል የሚል ለኦህዴድ/ብልጽግና ተጨማሪ እድሜ እንዲሰጠው ሽንጡን ገትሮ ይከራከራል። ለሱ ኦህዴድ/ብልጽግና እንደአንድ እግር ኳስ ቡድን የሚታይ ነው። አሁን የደከመው ቡድኑ ሳይሆን አንድ ተጫዋች ነው። አብይ አህመድ የሚባል የፊት አጥቂ ቡድኑን እያስበላ ነው። በእሱ ምክንያት የእግር ኳስ ቡድኑ ሊሸነፍና ከመድረክ ሊጠፋ ሆነ። ያ እንዳይሆን ነው ይህ ሁሉ ርብርብ ከጃዋር ሰፈር የደመቀው። ቡድኑ ከሚሸነፍ የተጫዋች ለውጥ ያስፈልጋል። 'ለዚህ እኔም ሆንኩ ሌሎች በተቀያሪ ወንበር ላይ ስላለን የእግር ኳስ ቡድኑን ከሽንፈት እናድነው' በሚል ሊገለጽ የሚችል አቋም በግልጽ ከጃዋር ይሰማል። አብይ አህመድን ዞር አድርገን ''ሀገረ መንግስቱ'' እንዳይፈርስ ''ስርዓተ መንግስቱን'' ከመናድ እንቆጠብ እያለን ነው። ህልሙ ያስፈራልና እንቅልፍ ይቅርብን እየተባለ ነው። ህልም ተፈርቶ መኝታ መሽሽ ያዋጣልን?
ለመሆኑ ወለጋ እንዳይኖር እየተገደለ ላለ ኢትዮጵያዊ፥ አዲስ አበባ ያንተ አይደለችም ተብሎ ለተፈናቀለና ወደ ቆሻሻ ለተወረወረ ዜጋ፥ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ለመንቀሳቀስ በህይወት ላይ ቁማር የመጫወት ያህል በሚታይባት ሀገረ ኢትዮጵያ፥ እዚህም እዚያም ዜጎች በህልወና አደጋ ውስጥ ገብተው በሚሰቃዩባት ምድር ፡ ሀገር የት ነው ያለችው? በእውን ሀገረ መንግስቱ አልፈረሰም? ምንድን ነው የቀረን?
እኔ የምለው
የአርበኛ ማርሸት ጸሀዩ ጉዳይ ብልጽግና ሰፈር ሰርግና ምላሽ የሆነበት ምክንያት የሚያስገርም ነው። ስለማርሸት የመጨረሻው መረጃ ምን እንደሆነ አላረጋገጥኩም። ባለኝ የቅርብ መረጃ ሰጪ የተረዳሁት ጉዳይ ቢኖር ብልጽግናዎች የሚያናፍሱት ነገር የተዛባ መሆኑን ነው። አርበኛ ማርሸት እጁን ሰጥቶ ይሁን ተይዞ በምንም መንገድ ቢሆን ብልጽግና ሰፈር መገኘቱ እንዲህ የሚያስፈነጥዝና ጮቤ የሚያስረግጠው ለምንድን ነው? ሄሊኮፕተር እያሳዩ እንደ አሜሪካውያኑ ማሪን ልዩ ኦፕሬሽን የሆሊውድ ፊልም የሚመስል ቀረጻ አድርጎ በማህበራዊ ሚዲያ መልቀቁ፥ በዚያ ደረጃ ብልጽግና ተንበቅብቋል ማለት ነው? ድል ሲጠማ፥ አሸናፊነት እንደሰማይ ሲርቅ እንዲህ ያደርጋል እንዴ? አርበኛ ማርሸት በትግሉ የነበረው ሚና ራሱን የቻለ ታሪክ ሆኖ ተሰንዶ ይቀመጣል፥ ከዚያ ባለፈ በህዝብ ትግል ላይ ምን የሚያጎድለው ነገር ኖሮ ነው እንደዚህ ዓይነት ልክ ያጣ ቸበርቻቻና ሪችት ማብራት?
ከላይ እንዳስቀመጥኩት የአርበኛ ማርሸት ጉዳይ ገና የመጨረሻውን ማረጋገጫ መረጃ እየጠበኩ ነው። አሁን ከሚናፈሰው የተለየ ነገር ሊሰማ እንደሚችል እገምታለሁ። ቢሆንም እንኳን ግን በዚያ ሰፈር እንዲህ የድል ከበሮ የሚያስደልቅ አይደለም። ለቆማጣ አንድ ጣት ብርቁ ናት እንዲሉ የሆነ የፋኖ አመራር በሆነ መንገድ እነሱ ሰፈር ሲመጣ ከበረት እንዳመለጠ ጥጃ የሚዘሉበት ነገር እጅግ አስደማሚ ነው። በነገራችን ላይ ትግሉ አሁን የደረሰበት ደረጃ ከእንዲህ ዓይነት ጉዳይ በብዙ ምዕራፎች ወደፊት ሄዷል። የፋኖ ትግል ከጎጃም በላይ ከአማራም በላይ ከፍ ያለ ማማ ላይ ወጥቷል። ቁመቱ ዘለግ ብሏል። ቀጠናዊ ገጽታን ተላብሷል። በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ የሚለካ አቅም ላይ ደርሷል። አከሌ አመራር ብልጽግና ገባ፥ ፋኖ እንትና እጅ ሰጠ የሚለው ብዙም ትርጉም በሌለው ሁኔታ ወደኋላ የተተወ፥ አሁን ባለው የፋኖ ቁመና ላይ የጭረት ያህል እንኳን ተጽዕኖ የማይፈጥር እንደሆነ ብልጽግናዎች ባይቀበሉትም መሬት ላይ ያለው እውነት የሚያረጋግጠው ይሄንኑ ነው። ከከዳ፥ እጅ ሰጠ ቅብርጥሶ ወሬ ተሻግሮ ትግሉ ሌላ ምዕራፍ ላይ ይገኛል። በፊትም እንደተባለው አዲስ አበባ አፍንጫ ስር ጫንጮም ተደርሶ የሚከዳ አመራር ቢኖር የህዝብ ትግልን የሚያቆመው ምድራዊ ሃይል ፈጽሞ አይኖርም። እናም ብልጽግናዎች በካፊያ አትራሱ። ፈንጠዚያችሁ ወደ ለቅሶ ይቀየር ዘንድ እነሆ ጊዜው ደርሷል።
ሌላው የጃዋር መሀመድ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ወንድም ምንም አልልም እያልኩ ለራሴ እምል እገዘትና መልሶ መሃላዬን የሚያስፈርስ የሆነ ነገር ይመጣል። ዛሬ ብልጽግናዎች የለቀቁትን የይልማ መርዳሳን ማሪን ኦፕሬሽን ክሊፕ ከአንድ ፌክ የፋኖ ደብዳቤ ጋር አውጥቶ ጉራውን ሲቸረችር አየሁትና ጾሜን አፈረስኩ። ጃዋር ተቻኩለህ ለህዝብ ከማጋራትህ በፊት በፋኖ ስም የወጣው ደብዳቤ እውነተኛ ስለመሆኑ ማረጋገጥ ይገባሃል። ቢያንስ ለተከታዮችህ ክብር እንዳለህ የምታሳየው ፌክ መረጃዎችን ባለማጋራት ነው። አጥንቱንም፥ ሾህናውንም ያገኘኸውን ሁሉ ገጽህ ላይ የምትሰቅል ከሆነ እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን ልንሸሽህ እንገደዳለን። ሙክት እየጠበቅን ቀንድና መንጋጭላ የምታቀርብልን ከሆነ ከአንተ ቤት ምን እንሰራለን?
የብልጽግናው አገዛዝ እስከአሁን ከፈጸመው የከፋ ሌላ አስከፊ ዕልቂት እየደገሰ መሆኑን አንድ ጥብቅ መረጃ ደርሶኛል። በወለጋ እየፈጸመ ባለው እጅግ አስደንጋጭና መጠነ ሰፊ ጭፍጨፋ የተነሳውን ህዝባዊ ቁጣ ለማስተንፈስ በሚል በደቡብ ወሎ ኦሮሞ ብሄር አስተዳደር ዞን የሰላማዊ የኦሮሞ ተወላጆች ግድያ እንዲፈጸም ድርጊቱንም የአማራ ፋኖ የፈጸመው እንደሆነ የሚያሳይ ሴራ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑን ነው መረጃው የሚያመለክተው። ከከባድ ጥንቃቄ ጋር መረጃውን ለህዝብ እንድናስተላልፈው የገለጹልን የብልጽግና ደህንነት ሰዎች የወለጋውን የአማራ ተወላጆች ጭፍጨፋ ከቁጥጥር ውጭ የሆነበት አገዛዙ በወሎ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ ዕልቂት ለመፈጸምና ፋኖን ተጠያቂ ለማድረግ በዚህም የእርስ በእርስ ዕልቂቱን ወደ ከፋ ደረጃ ለማድረስ ውስጥ ለውስጥ እየሰራበት ነው ብለዋል። አደገኛ ጊዜ ላይ ነን። አብይ አህመድ አጥፍቶ ለመጥፋት ተዘጋጅቷል። ወሎ አከባቢ ህዝቡ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በንቃት ይከታተል። ሁለቱም ማህበረሰቦች በጋራ የመጣባቸውን ይህን አስጨናቂና አደገኛ ጊዜ በጋራ ሊሻገሩት ካልቻሉ የመጣው አደጋ ከምንጊዜውም በላይ ከባድ ነው።
ጃዋር መሀመድ ማረፊያ አጣሁ፥ ከግራና ከቀኝ በጥፊ እያጮሉኝ ነው፥ እኔ እውነትን ብቻ በመያዜ ከወዲህ የፋኖ ደጋፊዎች፥ ከወዲያ የብልጽግና ነዋሪዎች በስድብ እያጥረገረጉኝ ነው ዓይነት ጨዋታ ጀምሯል። አደገኛ የሆነች ታክልም ገብቷል። ፋኖንና የአማራ ህዝብን ለማፋታት በሚል የወረወራት ሀሳብ በቅንነት ብቻ ለሚመለከት ሰው ገራገር ልትመስል ትችላለች። ግን እጅግ አደገኛ ናት። እኔ እስከሚገባኝና እስከማውቀው ፋኖ እንደህወሀትና እንደኦነግ በአንድ መነጽር የሚታይ አይደለም። ፋኖ የአሁኑ የፋኖ እንቅስቃሴ ከመጀመሩ በፊት የነበረ፥ የኖረ፥ በአማራ ብቻ ያልተገደበ፥ ለኢትዮጵያ ነጻነት ነፍጥ ያነሳ ሁሉ የሚጠራበት የወል ስም ነው። ከአማራም በላይ የኢትዮጵያንም ህዝብ የትግል መንፈስ የሚወክል ነው። አሁን ጫካ የወረዱት የአማራ ልጆች ያን መንፈስ ይዘው እንጂ እንደህወሀትና ኦነግ ድርጅት መስርተው አይደለም። የፋኖን መንፈስ እንኳን ከአማራ ህዝብ ከአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ህዝብ የምትነጥለው አይደለም። እኔ የፋኖን ትግል የምደግፈው በኢትዮጵያዊ ማንነት ላይ ቆሜ ነው። አይጋጭብኝም። የህወሀትና የኦነግ ታሪክ ሌላ ነው። መነሻቸውም መዳረሻቸውም ግልጽ ነው። እናም ጃዋር ፋኖንና የአማራን ህዝብ ለመነጠል የጀመርከው ጨዋታ አይነፋም። ፋኖን ጭራቅ አድርጎ ለመሳል ፈልገህ ከሆነ ብዙ ርቀት አይወስድህም።
ይህ የአንጋፋው ጋዜጠኛ ቅጣው ንጉሴ የዩቲዩብ ቻናል ነው። ጋዜጠኛ ቅጣው ከኤፍ ኤም 97 ምስረታ ጀምሮ በሚሰራቸው ለዛ ያላቸው ድንቅ ስራዎች የሚታወቅ፥ ለለፉት ከ20 በላይ ዓመታት በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በሙያው መልካም ስም በመያዝ የቆየ፥ አመለ ሸጋ ብርቱ ሰው ነው። ብዙ ቁምነገር የሚገኝበትን፥ በቀጣይም በፖለቲካው አቅጣጫ አያሌ ስራዎቹን የሚያቀርብበት ቻናል ያዘጋጀ ሲሆን ቤተሰብ ብትሆኑት የምታተርፉበት እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። በርታ ጋዜጠኛ ቅጣው ንጉሴ።
youtube.com/@yefiqirbet-tube…
እኔ የምለው
በወለጋ ሶስት መንደሮች ጥንቅቅ ብለው ወድመዋል። እስከአሁን ባለው መረጃ 400 የሚሆኑ የአማራ ተወላጆች ተገድለዋል። ከ300 በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል። ሶስት አብያተ ክርስቲያናት እንደጧፍ ነደዋል። ከ15ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተሰደዋል። በጉራጌ ጢያና ሱተን ተመሳሳይ የብሄርና የእምነት ማንነትን የለየ ጥቃት ተፈጽሟል። ጽንፈኛው የኦሮሞ ልሂቃን እሳቱን ካነደዱትና ኳሱን ወደ ሰማይ ጠልዘው ካጎኑት በኋላ የልብ ትርታ ለማዳመጥ የኋላ ወንበር ላይ ተቀመጠው ስለሆነው ሁሉ ማብራሪያ ሊሰጡን ዘለግ ያለ ጽሁፍ ይዘው መጥተዋል። ምንተፍረት የሚባል ነገር እንጦሮጦስ ወርዷል። ይሉኝታ ድራሽ አባቱ ጠፍቷል። ፍጥጥ ብሎ 'እኛ ከደሙ ንጹህ ነን። እናንተ ስንነግራችሁ አልሰማ ብላችሁ እንጂ'' የምትል ብልጣብልጥ መልዕክት እንዲደርሰን ተደርጓል። ክህደት የዘር ማጥፋት ድርጊት አንዱ መገለጫ መሆኑን ለሚያውቅ ብዙም አይደንቀውም። ይልቅስ የተለኮሰው እሳት መልሶ ራስን ሳያቃጥል በቶሎ መፍትሔ ቢፈልጉለት ጥሩ ነው። አዝማሚያው ያስፈራል። ዳር ሆነው ከእሳቱ መሞቅ ለጊዜው ሊመስል ይችላል። ነገ የሚሆነውን ዛሬ እርግጠኛ መሆን ይከብዳል። ኳስ በመሬት እንዲያደርጉት መሀል ያላችሁ ሰዎች እስቲ ምከሯቸው።
የኦነጉ ቀጄላ መርዳሳ ሰሞኑን ተፈትቶ ተለቋል። ይህ ሰው መቼ እንደሚረጋጋ የሚታወቅ ነገር የለም። ሶስተኛ ጸጉር አብቅሎ አሁንም እንደሰፈር ጢቦ ነው የሚያወራው። በስተርጅና መጃጃልን ለምን እንደፈለገው አላውቅም። አህያ ሳይኖረው ፈረስ ይንቃል። የኢትዮጵያን ታሪክ ደብተራ የጻፈው ነው እያለ የተለመደውን አርቲ ቡርቲ ቀብረር ብሎ ያወራል። የእሱን ተረት ተረት የሚደግፍ አንድ የታሪክ ማስረጃ አያቀርብም። እሱ ስለሚለው ትርክት ማረጋገጫ የሚሰጥ አንድ መጽሀፍም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ የታሪክ ሰነድ አይነግረንም። ዝም ብሎ ''ይሄ የደብተራ ታሪክ ነው፡ ይሄ የነገስታት ዜና መዋዕል ነው'' እያለ ማጣጣልና ማራከስ እውቀት አድርጎት ረጅም ሰዓት ያወራል። ሌላውን ማስረጃ ውድቅ ለማድረግ ያንተ ደጋፊ ሰነድ ምንድን ነው ሲሉት ሜጫ የኦሮሞ ስም ነው፥ ጋና ቃሉ የኦሮምኛ ነው፥ እያለ ለህጻናት እንኳን የማይነገር እንቶ ፈንቶ ይቀባጥራል። መቼ ነው ይህ ሰው የሚበስለው? ለነገሩ አብዛኛው የኦሮሞ ጽንፈኛ ልሂቃን ታሪክን ከወገቡ ይጀምሩና ጥላቻና መርዝ ለውሰው አይናቸውን አፍጥጠው መናገር እንጂ አንድም ደጋፊ የሆነ ማስረጃ ሲያቀርቡ አይተንም ሰምተንም አናውቅም። ኦቦ ቀጄላ እባክዎን ይረጋጉ። ለነገው ትውልድ መኖሪያ አያሳጡት። በማምሻ እድሜዎ የጎረምሳ ባህሪ ጥሩ አይደለም። ከሰውም ከፈጣሪም ተጣልተው ምን ያተርፋሉ?!
ወለጋ በቆዳ ስፋት ከሩዋንዳ ትበልጣለች። አሁን የሩዋንዳን አይነት የዘር ፍጅት በማስተናገድ ደግሞ ሌላ የምትበልጥበትን ታሪክ እያስመዘገበች ነው። የቤተክርስቲያን ካህናት የተክህኖ ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ተደርገው ራቁታቸውን እየተረሸኑ ነው። ምንም የቆመ ነገር ካለ ይቃጠላል። ይፈርሳል። ነፍስ ያለው ፍጡር ከተገኘ ይገደላል። እንስሳትም ሳይቀሩ።
ወለጋ የአማራ ተወላጆች መገደያ ቄራ ሆናለች። ተመሳሳይ ዕልቂት በጉራጌ ዞን አንዳንድ አከባቢዎች እየተከሰተ ነው። ይህን የሚያደርገው የዳቦ ስም የተሰጠው ኦነግ ሸኔ እንዳይመስላችሁ። አሁን ማስመሰሉን፥ ድራማውን ትተው በፊት ለፊት ራሳቸው ነው እያደረጉት ያሉት። የኦሮሚያ ልዩ ሃይል፥ የገዳ ኮማንዶ፥ የኦሮሚያ ሚሊሺያ፥ ጋቸና ሲርና፥ ኤርጴ ሎላ፥ ኮሬ ነጌኛ፥ አባ ቶርቤ፥ ዝርዝሩ ይቀጥላል። መከላከያ ሰራዊት የተባለው የአብይ ዘብ ደግሞ በቅርብ ርቀት ያግዛቸዋል። ስማቸው የተለያየ ግብራቸው ግን አንድ የሆነ፥ በአንድ የዕዝ ሰንሰለት የሚመሩ፥ ከአንድ አካል ቀለብና ስንቅ የሚሰፈርላቸው የጸጥታ መዋቅሮች ናቸው።
ይህን ታላቅ ሰበዓዊ ዕልቂት በ21ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጵያ ምድር ላይ ሲከናወን እነጃዋር መሀመድ ''የፍየሏን ለቅሶ'' ማቅለጥን ስራቸው አድርገው ተያይዘውታል። ጃዋር በይፋዊ ገጹና በሌላ አካውንቱ Finfinne Press John የወለጋውን ዕልቂት ለማድበስበስና በሌላ አጀንዳ ለመጥመድ በሳምንት ለሰባት ቀናት በቀን ለ24 ሰዓታት እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ነው። እንደጅራፍ ራሳቸው ገርፈው ራሳቸው እየጮሁ ነው። አሁን ነገሮች ግልጥልጥ ብለዋል። እየሆነ ያለውን ሁሉ ታሪክ እየመዘገበ ነው። ነገ የፍትህ ቀን ይመጣል።
የብልጽግና መንደር በእስክንድር ነጋ የዛሬው መግለጫ ጮቤ ሲረግጥ ውሏል። የትብብሩ መምጣት እንቅልፍ የነሳቸውም እስከንድር ነጋን ''አበጀህ፥ ግፋበት'' እያሉት ናቸው። የእስክንድር ነጋ ጉዳይ በቤተሰብ ታይቶ መፍትሔ የሚገኝለትና እየተገኘለትም ያለ በመሆኑ የጬሰው አቧራ ነገ ከነገ ወዲያ ይሰክናል። ትብብሩ ለሚያቃዣቸው ከግራም ከቀኝም ላሉ አካላት ማለት የሚቻለው ነገር ቢኖር የማይመለስ ሃይል መንገድ ጀምሯል። በእናንተ ጩኸት፥ በየትኛውም ሴራችሁ ፥ ከሰማይ ወደ ምድር ብትፈርጡ እንኳን ለአንዲት ስንዝር ወደ ኋላ አይመለስም። በደንብ ጩኹና ይውጣላችሁ። ሙሽሮች እየመጡ ነው። ኢትዮጵያ ሰርገኛውን መቀበሏና ቅልጥ ያለ የነጻነት ድግስ በቅርቡ እንደሚኖር ግን ቅንጣት ታክል መጠራጠር አያስፈልግም። ለኢትዮጵያውያን ብስራት፥ ለብልጽግናው መንደር መርዶ በቅርቡ ከጆሮ የሚደርስ ይመስለኛል።
ጃዋርን በተመለከተ ብዙም ማለት አልፈልግም። እርሳሱ ያለቀ የጥይት ቀለሀ የሚመስለኝ እኔን ብቻ ይሆን? ጃዋር ወደ ኋላ መመለስን ምርጫው አድርጓል። በፌስቡክ፥ በዩቲዩብ፥ በቲክታክ፥ በኢንስታግራም፥ በቴሌግራም፥ በኤሮግራም የቀረው ፕላትፎርም የለም። መጉላት አቅቶታል። እርሳሱን ስለጨረሰ ቀለሃው ይጮሃል እንጂ ዒላማውን አይመታም። ጃዋር ከአጀንዳ ላለመውጣት እልህ አስጨራሽ ግብግብ ላይ ነው። ትኩረት ተርቧል። ርዕሰ ጉዳይ መሆንን በእጅጉን ተጠምቷል። ትላንት የሚያሸበሽቡለት ቁጥራቸው በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። መሪውን አዙሮ ወደ አብይ መንደር እየገባ ነው የሚሉ ሰዎችን እሰማለሁ። የጃዋር ምርጫ ያ ከሆነ በገዛ እጅ ሞትን ራስ ላይ የመፍቀድ ታሪካዊ ስህተት ይሆንበታል። ለጃዋር የሚበጀው ጥሞና ነው። እረፍት ያስፈልገዋል። ሀኪሙ ለምን በዚህ ደረጃ ዝም እንዳለው አላውቅም። ብዙ እረፍት፥ ብዙ ማዳመጥ፥ ብዙ መስከን፥ ለጃዋር ጤንነትም ሆነ ቀጣይ የፖለቲካ ህይወት ፍቱን መድሃኒቶች ናቸው።
ለአንድ የቤተሰብ ጉዳይ ዞር ብዬ ስመለስ ይህቺ መንደር የቀለጠ ሆና ጠበቀችን። ጃዋር መሀመድ በይፋዊ ገጹና በሌላኛው አካውንቱ Finfinne Press John ሙድ ይዞ በፉገራ ሲያጥረገርገኝ ያየሁት አሁን ከደቂቃዎች በፊት ነው። ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዲሉ የመርካቶው ኪስ አውላቂም ሰሞኑን እንደጀርባ ቅማሉ ጠምዶ ስሜን በየሰዓቱ እያነሳ ሲሞልጨኝ እንደነበረ ያወኩትም አሁን ነው። እስክንድር ነጋ 'ጽምዶን' እንደ አባቱ ገዳይ ቂም እንደያዘበት ለጀርመን ሬዲዮ መናገሩን የሰማሁት ከሰከንዶች በፊት ነው። እስቲ አሁንም መንደሩን ጎብኘት ማድረጌን ልቀጥል። ለጃዋር ግን አንዲት የቀረችኝን መልዕክት አደርስለታለሁ። እንካሰላንቲያው ተገቢ እንዳልሆነ ባምንም 10 ተኩሶ 1 የአጸፋ ተኩስ መመለስ ግን ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ። ጃዋር ያስፈልገናል። እንደጎረምሳ የሚያደርገውን ይህቺን ባህሪውን ከተወ ለሀገር የሚጠቅም አቅም ያለው እንደሆነ ልነግረው እፈልጋለሁ። ለማንኛውም ሌላ ነገር ካለ ዞር ዞር ብዬ ላፈላልግ። ደሀና ውሻ የሚያምርባቸውም ዞር ዞር ሲሉ ነው😀😃😄
የአብይ አህመድ በዛሬው የምክክር ኮሚሽን የማጠቃለያ መርሃግብር ላይ አለመገኘት እንደተራ ክስተት ማየት የሚገባ አይመስለኝም። ባኞ ቤት ተሰራ፥ ሽንት ቤት ተገነባ ብሎ ለምርቃቱ ጀሌውን አንጋግቶ የሚሄደውና ለቴሌቪዥንና ፎቶግራፍ ቀረጻ ጥንቅቅ ብሎ የሚቀርበው አብይ አህመድ በዚህ የአገዛዙ ትልቅ ድግስ ላይ አለመገኘቱ በሌላ ጉዳይ ተጠምዶ ነው የሚለው ሰብብ ምክንያት ማንንም የሚያሳምን አይደለም። ከእሱና ከሚስቱ በስተቀር ሁሉም ጀሌዎቹ አዳራሹ ውስጥ ነበሩ። ደግሞ መርቆ የከፈተው መድረክን መዝጋት የነበረበት እሱ መሆን ነበረበት። እንደሰማሁት በመርሃ ግብሩ ላይ የእሱ መገኘት ተጠቅሶ ነበር። ግን አብይ አህመድ የለም። የት ሄዶ? እሱን የበላ ጅብ ካለስ ለምን አልጮኸም?
አንዳንድ ሹክሹክታዎች የሰውዬውን መታመም የሚያሳዩ ናቸው። ቢሮው ከታየም 10 ቀናት እንዳለፉትም ይነገራል። ያለወትሮውም በቴሌቪዥን ስክሪን ላይ የማይጠፋው አብይ አህመድ በዚህ የአገዛዙ ትልቅ መድረክ ላይ አለመታየቱ ጥርጣሬዎችን እንድናጤናቸው ያደርጉናል። አብይ ታማሚ እንደሆነ ከግምት በላይ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከጭንቅላቱ የኋላ ክፍል ጋር በተያያዘ በየጊዜው ለህክምና ውጭ ሀገር እንደሚመላለስ በቅርበት የማውቀው መረጃ አለኝ። ታዬ ደንደአ ከመታሰሩ በፊት በነበረን የስልክ ቆይታ አንድ ቀን የገጠመውን አጫውቶኛል። አብይ አህመድ ውጭ ሀገር ለህክምና ቆይቶ ሲመለስ ከሽመልስ አብዲሳ ጋር በተፈጠረ የክረረ አለመግባባት የተነሳ ሊያናግረው ቤተመንግስት ጠርቶት ነበር። አብይ የሰውን አእምሮ ለመቆጣጠር የሚጠቀማቸው ስልቶችን ታዬ ደንደአ ጠንቅቆ እንደሚያውቅ ገለጸልኛና በቤተመንግስት ቆይታውም አብይ አህመድ ኮቱን አውልቆ ሸሚዙንም ቁልፉን ፈትቶ ጀርባውን ለታዬ ያሳየዋል። ከወገቡ ጀምሮ እስከ ኋለኛ የጭንቅላቱ ክፍል ድረስ በፋሻ ተጠቅልሏል። ከበድ ያለ ህክምና አደርጎ እንደተመለሰ ለታዬ ነገረው። ጭንቅላቱን ለመስለብና ታዬ አርፎ እንዲቀመጥ ለማድረግ እንዲህ ዓይነቱን ታክቲክ እንደሚጠቀም ታዬ አውቆ ነበርና ብዙም አልደነገጠም። ለማንኛውም አብይ አህመድ ጽኑ በሆነና ከአንጎል ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ውስጥ እንዳለ ታዬ በወቅቱ አጫውቶኝ ነበር። በቅርቡም ዶ/ር ሚልኬሳ ሚደጋ ባጋራን መረጃ አብይ አህመድ በየጊዜው ከኋላው የጭንቅላቱ ክፍል ደም የሚቀዳ እንደሆነ በዚህም ከአንድ ወር በፊት ለዚሁ ህክምና ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ እንደነበር ገልጾልናል። በአንድ ወር ልዩነት አብይ አህመድ ወደዚያ ህክምና ሄዶ ሊሆን እንደሚችል ከጥርጣሬም በላይ መግለጽ ይቻላል።
ይህ ሁኔታ የመለስ ዜናዊን የመጨረሻ ሳምንታት አስታወሰኝ። መልስ ዜናዊ በጭንቅላት ካንሰር ይታመም ነበርና ኢሳት ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች የአቶ መለስ ዜናዊን የጤና ሁኔታ በየጊዜው እየተከታተለ ለተመልካቹ ያቀርብ ነበር። ሀምሌ 21 በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2004 ዓመተ ምህረት መለስ ዜናዊ ህይወቱ አለፈ። መረጃው ለኢሳት ደርሶት ከማንም አስቀድሞ የመለስ ዜናዊ ህልፈት ይፋ አደረገ። በወቅቱ የህወሀት/ኢህ አዴግ መንግስት መለስ ዜናዊ ለስራ ጉዳይ በውጭ ሀገር እንደሚገኝ በመግለጽ ከፍተኛ የመረጃ ማዛባት ዘመቻ ላይ ተጠምዶ ነበር። በረከት ስምዖን እንደውም ለእንቁጣጣሽ ጠብቁት ይመጣል የሚል መግለጫ ሰጠ። መለስ ዜናዊ በዚያን ጊዜ በብራስልስ የአስክሬን ማረፊያ ሞርግ ውስጥ ነበር። በዚያን ሰሞን የአፍሪካ ህበረት ወሳኝ ስብሰባ በአዲስ አበባ ይካሄድ ነበርና የወቅቱ የህብረቱ ሊቀመንበር የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ''ወንድማችን መለስ ዜናዊ ከአጠጋባችን ባለመኖሩ እናዝናለን'' ሲሉ ተናገሩ። ህወሀት/ኢህ አዴግ የደበቀውን ሚስጢር ማኪ ሳል አፍረጠረጡት። ይህን የማኪ ሳልን መግለጫ ለማስተባበል በወቅቱ የህወሀት/ኢህ አዴግ አገዛዝ መጠነ ሰፊ የመግለጫ ጋጋት ሲያቀርብ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ከአንድ ወር በኋላ የመልስ ዜናዊ ህለፈት በብሄራዊ ቴሌቪዥን ይፋ ተደረገ።
የሰሞኑ የአብይ አህመድ ከሚዲያና ከመድረኮች መጥፋት ያን ወቅት አስታወሰኝ። ለምን እንደሆነ አላውቅም። ግን አብይ አህመድ የት ነው? መደበኛውን የጤና ህክምና ክትትል ሊያደርግ ወይስ ከዚያ የከፋ ነገር ይኖር ይሆን? መጠርጠራችን ስህተት አይደለም። የሀገር መሪ ነውና ከዛሬው ዓይነት መድረክ ሲጠፋብን ጊዜ አሳሰበንና ነው ይህቺ የለቀለቅነው📷📷📷